Revelation of John 15

ሰባቱ መላእክትና ሰባቱ መቅሠፍቶች

1ሌላም ታላቅና አስደናቂ ምልክት በሰማይ አየሁ፤ የመጨረሻዎቹን ሰባት መቅሠፍቶች የያዙ ሰባት መላእክት አየሁ፤ የመጨረሻ የተባሉትም የእግዚአብሔር ቍጣ የሚፈጸመው በእነርሱ በመሆኑ ነው። 2ከእሳት ጋር የተቀላቀለ የብርጭቆ ባሕር የሚመስል አየሁ፤ በባሕሩም አጠገብ አውሬውን፣ ምስሉንና የስሙን ቍጥር ድል የነሡትን ቆመው አየሁ፤ እነርሱም ከእግዚአብሔር የተሰጣቸውን በገና ይዘው፣ 3የእግዚአብሔር ባሪያ የሆነውን የሙሴን መዝሙርና የበጉን መዝሙር እንዲህ እያሉ ይዘምሩ ነበር፤

“ሁሉን ቻይ ጌታ አምላክ ሆይ፤
ሥራህ ታላቅና አስደናቂ ነው።
የዘመናት
አንዳንድ የጥንት ቅጆች ሕዝቦች ይላሉ።
ንጉሥ ሆይ፤
መንገድህ ጽድቅና እውነት ነው።
4ጌታ ሆይ፤ አንተን የማይፈራ፣
ስምህን የማያከብርስ ማን ነው?
አንተ ብቻ ቅዱስ ነህና።
የጽድቅ ሥራህ ስለ ተገለጠ፣
ሕዝቦች ሁሉ ይመጣሉ፤
በፊትህም ይሰግዳሉ።”
5ከዚህ በኋላም አየሁ፤ በሰማይ ያለው ቤተ መቅደስ፣ ይኸውም የምስክሩ ድንኳን ተከፍቶ ነበር። 6ሰባቱን መቅሠፍቶች የያዙት ሰባቱ መላእክት ከቤተ መቅደሱ ወጡ፤ እነርሱም ከተልባ እግር የተሠራ ንጹሕ የሚያበራ ልብስ ለብሰው፣ ደረታቸውንም በወርቅ መታጠቂያ ታጥቀው ነበር። 7ከዚያም ከአራቱ ሕያዋን ፍጡራን አንዱ ከዘላለም እስከ ዘላለም በሚኖረው አምላክ ቍጣ የተሞሉትን ሰባት የወርቅ ጽዋዎች ለሰባቱ መላእክት ሰጣቸው። 8ቤተ መቅደሱም ከእግዚአብሔር ክብር፣ ከኀይሉም በወጣው ጢስ ተሞላ፤ የሰባቱ መላእክት ሰባት መቅሠፍቶች እስኪፈጸሙ ድረስ ማንም ወደ ቤተ መቅደሱ መግባት አልቻለም።

Copyright information for AmhNASV